ከሰላም እንጂ ከግጭት ያተረፈ ቢኖር የጦር መሳሪያ ነጋዴ ብቻ ነው !!

ከሰላም እንጂ ከግጭት ያተረፈ ቢኖር የጦር መሳሪያ ነጋዴ ብቻ ነው !!

የደቡብ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳው በ08/03/2012 ዓ/ም በደቡበ ኦሞ ዞን ባደረጉት የመስክ ጉብኝት የጂንካ ዩንቨርሲቲ ተማሪዎችን በሰላም ዙሪያ አነጋግረዋል፡፡ በዚሁ ወቅት የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አሁን ላይ ሌሎች አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ካሉበት የሰላም ውጥረት አኳያ ዕድለኞች ናችሁ ያሉት የደቡብ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳው ተማሪዎች በራሳችሁ አንደበት እንደመሰከራችሁት ፍፁም ሰላም ከሆነችው ጂንካ ለምን ወደ ግጭትና ዓላማ-ቢስነት ለሚገፋፋን ኃይል ዕድል እንሰጣለን?”ብላችሁ እራሳችሁን በመጠየቅ ቆም ብላችሁ ልታስቡ ይገባልም ብለዋል፡፡ ይልቁንም ተማሪዎቹ የራሳቸዉንና የቤተሰባቸዉን ዕድል ላለማጨለም ይህንን እኩይ ተግባር የሚፈፅሙትን በማጋለጥና በማውገዝ እንዲሁም ቤተሰቦቻቸዉን በማረጋጋት በዩኒቨርስቲው ባለው የተሻለ ሰላም ተጠቅመው ትምህርታቸዉን እንዲከታተሉም ም/ ር/መስተዳድሩ አቶ እርስቱ ይርዳው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ፕሮፌሰር ገብሬ ይንቲሶ በበኩላቸው የዩኒቨርሲቲያችን ሰላም መሆን ያልተዋጠላቸው የፀረ-ሰላም ኃይሎች ተልዕኮን ለማሳካት የሚሯሯጡ በጣት የሚቆጠሩ ግለሰቦች በተማሪዎቻችንና በወላጆቻቸዉ ላይ የስነ-ልቦና ጫና ለማሳደር ጥረት እያደረጉ ይገኛል ብለዋል። በጥፋተኞች ላይ የዲስፕሊን እርምጃ እንደሚወሰድ ጠቅሰው ተማሪዎች በውሸት ሳይሸበሩ ተረጋግተው እንዲማሩና ወሬኞችን እንድያጋልጡ መክረዋል፡፡

ተማሪዎቹ ከር/መስተዳድሩ ጋር ባደረጉት ውይይት ወቅት በሰጡት አስተያየት እንደገለጹት የጂንካ ህዝብ ለዩኒቨርሲቲው ተማሪ ያለው አቀባበልና ያሳየው ፍቅር አይረሴ ቢሆንም በሀገሪቱ ባሉ አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ከሚስተዋሉ የሰላም ውጥረቶች የተነሳ በራሳቸዉና በወላጆቻቸው ዘንድ የተፈጠረው ስጋት እንዲቀረፍላቸው ጠይቀዋል። ለተነሱት ጥያቄዎች በር/መስተዳድሩና በዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት በኩል በተሰጡ ምላሾች በመግባባት ውይይቱ ተጠናቋል፡፡